የውሃ አገልግሎቶች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት አደረጃጀት መገንባቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና አለው ተባለ።

የውሃ አገልግሎቶች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት አደረጃጀት መገንባቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና አለው ተባለ። አዳማ : ሰኔ 06/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃ አገልግሎቶች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት አደረጃጀት መገንባቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል። የውሃ አገልግሎቶችን አቅም ለማሳደግ የከተሞች ውሃና ሳኒቴሽን ፌደሬሽን ከዩኒሴፍ ጋር አዘጋጅተውት ለ5 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ያነጋገርናቸው የፌደሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙክታር አህመድ በቂ፣ ዘላቂ፣ ጥራት ያለው ፣ የዘመነና የደንበኞችን ፍላጎት ያረጋገጠ የውሃ አገልግሎት ለመገንባት የተፈጠረው አደረጃጀት ወሳኝ ነው ብለዋል። ፌደሬሽኑ ጠንከር ያሉ አገልግሎቶች የራሳቸውን አቅም እያሳደጉ ደከም ያሉትን የሚደግፍበት በስልጠና የታገዘ አሰራር ተቋማዊ በሆነ መንገድ ተዘርግቶ ሁሉም አገልግሎቶች ተቀራራቢ ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል። አደረጃጀቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ከቴክኖሎጂ፣ ከውሃ ታሪፍ ፣ከብክነትና ከማይከፈልበት ውሃ ጋር ተያያዠ የሆኑና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል። የባህርዳር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለሙ አደረጃጀቱ በሀሳብ ፣ በስልጠና ፣ በልምድ ልውውጥና በቁሳቁስ እንድንደጋገፍና ወደ የአካባቢያችን ነባራዊ ሁኔታ ወስደን በመተግበር በአነስተኛ ወጭ ውጤታማ ስራ ሰርተን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንድናረጋግጥ ይረዳናል ብለዋል። እንደ ከተማ 35 የውሃ ተቋማት እንዳሉ የጠቀሱት ዋና ስራ አስኪያጁ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁለት የውሃ ተቋማትን ገንብተው የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ሽፋናቸውም 73 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። የውሃ ስራ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚቆም አይደለም የሚሉት ስራ አስኪያጁ የከተማ መስፋፋት እና ተያያዠ በሆኑ ጉዳዮች አገልግሎታችን ለማስፋት በተያዘው አመት በ200 ሚሊየን ብር 4 የውሃ ጉድጓዶችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። ከፍሳሽ አገልግሎት አኳያም ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ 102 የጋራና የህዝብ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። ህብረተሰቡ ያልተሳተፈበት ስራ ዘላቂነት አይኖረውም ያሉት ስራ አስኪያጁ ህገ ወጥ ስራዎችን በማጋለጥ፣ ውሃ ሲባክን በመጠቆምና የባለቤትነት ስሜት በመውሰድ ማንኛውም አካል ከውሃ አገልግሎት ጎን እንዲቆምም አደራ ብለዋል። ቴክኖሎጅና የውሃ አገልግሎቶች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ያሉት የጅማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምናዋር ሁሴን ብክነትን በመቀነስ ፣ የፋይናንስ አቅምን በማሳደግ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት ና የተጠቃሚውን ጊዜና እንግልት ለመቀነስ ሁሉም የውሃ አገልግሎቶች በቴክኖሎጅ የተደገፈ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፤ ለዚህ ደግሞ የሚሰጡ ስልጠናዎች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ልክ እንደ ባንክና ቴሌኮም የውሃ አገልግሎቶች ወጥ የሆነ አሰራርና አፈጻጸም እንዲኖራቸው እና ሲስተሙ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወስድ እንደሚገባም ጠቁመዋል። እንደ ከተማም 31ሺ 500ሜትር ኪዮብ ውሃ በየቀኑ እንደሚያቀርቡና ሽፋናቸውም 93.5 በመቶ መሆኑን ገልጸውልናል። የአክሱም ውሃ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ብሩ ከጦርነቱ በኋላ የውሃ አገልግሎቱ በማገገም ላይ ያለ እና መነቃቃት የታየበት እንደመሆኑ የተፈጠረው የመደጋገፍ አደረጃጀት በእጅጉ ያግዘናል ብለዋል። አክሱም የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ ይህንን በሚመጥን መልኩ የውሃ አቅርቦቱ ላይ የመንግስትና የአጋር ድርጅቶችን ትኩረት እንደምትሻም ጠቁመዋል። እንደ ከተማም የውሃ ሽፋኑ 18.7በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

Share this Post