የራሳቸውን አቅም እያጎለበቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የውሃ አገልግሎቶች እየተገነቡ መሆኑ ተገለጸ።
አዳማ : ሰኔ 3/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የራሳቸውን አቅም እያጎለበቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የውሃ አገልግሎቶች እየተገነቡ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገልጸዋል።
ክቡር አምባሳደሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የውሃ አገልግሎቶች በፋይናንስ ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ፣ የዘመነ ቴክኖሎጅ በመጠቀምና የተሻለ የሰው ሀይል በማልማት የበቁ የውሃ አገልግሎቶች ሌሎችን እያገዙ እንዲያበቁ የማድረግ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን ፌደሬሽንም የውሃ አገልግሎቶችን አቅም ለማሳደግ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በዩኒሴፍና አለም አቀፍ የውሃ አሊያንስ በኩል በሚደረግ ድጋፍ ጠንካራ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጥቅም ላይ ከሚውለው ውሃ 39 በመቶ የሚሆነው ይባክናል ያሉት ክቡር አምባሳደሩ የቧንቧዎች ማርጀት፣ ህገ ወጥ የመስመር ዝርጋታና ገንዘብ የማይከፈልባቸው ውሃዎች እና ተያያዠ ጉዳዮች ምክንያቶቹ ናቸው ብለዋል።
ይህንን በማሻሻል የሚባክነውን ውሃ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ባንቧዎችን የማደስ ፣ ዘመናዊ የውሃ ቆጣሪ የመግጠም፣ የገንዘብ አከፋፈልን ስርአትን ዲጅታላይዝ የማድረግ ፣ የታሪፍ ማሻሻያ እና የጅአይ ኤስ ሲስተምን ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎቱን በስፋት በማዳረስ የውሃ አገልግሎቶች የጥገናና ሌሎች ወጭዎቻቸውን ከመሸፈን ባለፈ የገቢ አማራጮችን እንዲያስቡ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ አዳማ ፣ ባህር ዳር ፣ሀዋሳ እና ጅማ ያሉ ከተሞች የውሃ አገልግሎቶች ሌሎች ትናንሽ ከተሞችን እንዲያበቁ እና ራሳቸውን የሚገነቡ ተቋማት ለመፍጠር አሊያንስ ተፈጥሮ ሌላው አለም ከደረሠበት ደረጃ ለመድረስ እና ተወዳዳሪ ለመሆን ከፖለቲካ አመራሩና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ክቡር አምባሳደሩ አክለዋል።
እንደ ሀገር ወጥ የሆነ የቦርድ እና የውሃ አገልግሎቶች አደረጃጀት እንደ ህዝብ ቁጥራቸው እና እንደአገልግሎት አሰጣጣቸው ለመፍጠር ብቃት ባላቸው አመራሮች እንዲመራ በማድረግ የህዝባችን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰፊ ስራ ለመስራት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበትም ብለዋል።