በመጪው የክረምት ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖራቸው ተጠቆመ።

በመጪው የክረምት ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖራቸው ተጠቆመ። ግንቦት 15/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በአዳማ ባዘጋጀው መድረክ በመጪው የክረምት ወቅት የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖር ተጠቁሟል። መርሀ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት በተሻለ ብቃት ለመወጣት ከልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት የማስፈፀም አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የአጭር ፣የመካከለኛ የረጅም ጊዜ የአየር ሁኔታና ጠባይ ትንበያዎችን፣ ሳይንሳዊ ልኬቶችን በማዘጋጀት ለግብርና፣ለኢነርጂ፣ ለጤና እና ለአቪየሽን የሚትዎሮሎጂ ትንበያ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እየሰጠ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል። መርሀ ግብሩ ኢንስቲትዩቱ ይፋ የሚያደርገውን የቀጣይ ክረምት ወራት የአየር ጠባይ ትንበያ የአጭር፣መካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ትንበያዎችን መሠረት በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች የመከላከል እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን በመስራት ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ትንበያውን መጠቀም እና የሚጠበቅብንን መወጣት እንደሚገባ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አሳስበዋል። በመርሀ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የአለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ ተቋሙ በ11ክልሎች የሜትሪዎሎጂ ማእከል በማደራጀትና ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመትከል እለታዊና የረጅም ጊዜ ትንበያ አገልግሎት በመስጠጥ ውጤታማ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በመጪው የክረምት ወቅት አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ በመጭው የክረምት ወቅት በየ10 ቀኑ የሚሰጠውን ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሠረት በማድረግ ሁሉም አካላት ህይወትንና ንብረትን ከአደጋ መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

Share this Post