በቦረና ዞን የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

በቦረና ዞን የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። መጋቢት 18/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል 100 ኩዩቢክ ሜትር ሪዘርቬየር ያለው የሮምሶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ106 ሚሊየን 300 ሺ ብር በላይ በሚሆን ወጭ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ፕሮጀክቱ ከ4ሺ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችንና ከ27ሺ በላይ የሚሆኑ እንስሳቶችን ውሃ ያጠጣልም ተብሏል፥። የቦረና ዞን ም/ አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ጋኖ እንደ ዞን በስድስት ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፕሮጀክቱ ድርቅ ቢከሰት ህብረተሰቡ እንዳይፈናቀልና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ሚናው ላቅ ያለ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊመሠገን ይገባል ብለዋል። የአካባቢው ነዋሪ የሆነችው ኤሌማ ሮባ ከዚህ ቀደም ውሃ ለመቅዳት የምትጓዝበትን ርቀትና የነበረውን ችግር አስታውሳ አሁን ላይ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ መገንባቱ ኑሯአቸውን ከማቅለሉም በላይ ከብቶቻቸውንም ውሃ የሚያጠጡበት ሁኔታ በመፈጠሩ በእጅጉ መደሰቷን ገልጻ የመጠጥ ውሃውን ላቀረበላቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ምስጋና አቅርባለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና በቦረና ዞን 300 ሜትር ኪዩብ ሪዘርቬር ያለው ፣ ከስምንት ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው እና ከ 133 ሚሊየን 231ብር በላይ ወጭ እየተገነባ ያለው የዲዳ ያቤሎ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ታውቋል። በተመሳሳይ የኤርደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ83 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ ተገንብቶ ከ2,400 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሆኖ አምስት ቦኖዎች፣ ሶስት የከብቶችና ሁለት የፍየል ማጠጫ ገንዳዎችንም አካቷል። ፕሮጀክቱ በአንድ ሳምንት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል። ሁሉም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በሶላር ኢነርጂ የሚሰሩ ናቸው።

Share this Post