የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ፡፡

ሚያዚያ /2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ሴክሬተሪያት ከቁልፍ ባለድርሻ አካት ጋር አዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል ውይይት ተደረገ፡፡

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ኢትዮጵያ እንደሀገር የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭን ከመመስረት ባለፈ የናይል ቤዚን ሀገራት በውሃ ሀብቱ የጋራ ጥቅም እንዲኖራቸው ታላሚ ያደረገውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የመጀመሪያዋ ፈራሚ እና በፓርላማዋ ያጸደቀች ሀገር ናት ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ10 ዓመት እቅዳችን መሰረት በናይል ቤዚን ላይ እንደሀገር መጠቀም ካለብን በርካታ ነገሮች ውስጥ በኢነርጂ ዋስትና፣ በምግብ ዋስትና፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ድንበር ተሸጋሪ የውሃ ሀብት አጠቃቀማችን ላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በቤዚኑ ላይ መጠቀም ያለባትን አስቀምጣለች፤ በዚህም መሰረት በተወሰኑ አካቢዎች ላይ የመስኖ ልማት እንዲሁም በሀይል ዘርፉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመስራት ጅማሮ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር እስካሁን በቤዚኑ በታሰበው ልክ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመናል ብለን አናስብም የሚሉት ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው መስራት ያለብንን ስራዎች እንድንሰራ የሚያስችል መደላድል ግን ፈጥረናል ብለዋል፡፡

የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራት ሲፈርሙ የውሃ ሀብታችን ማንንም ሳንጎዳ በጋራ የምንጠቀምበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የመድረኩ ዋና ዓላማም እንደሀገር አጋር አካላቶቻችን በናይል ቤዚን ላይ ምን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ነበር፤ በቀጣይ ምን ሊያደርጉ ይገባል፤ በውሃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችን ማስከበር ላይ የባለድርሻ አካላት ተሳፈትፎ ምን ሊሆን እንደሚችል ትኩረት የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት እንደሀገር የአረንጓዴ አሻራ እና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎቻችን በታችኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ሊኖር የሚችለውን የውሃ ሀብት የሚያስተካክል እንደሆነና ይህ የሚሆነው ደግሞ የጋራ ኮሚሽን አቋቁመን ስንሰራና ውሃን የመጠቀም መብታችን በጋራ ስናስከብር ነው ብለዋል፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሎሬንስ አዶንጎ እንዳሉት የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ከተመሰረተ 25 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ጠቅሰዉ፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ በማልማት፣ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማመቻቸት እና የውሃ ሀብቶች ልማት ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጠናው ያሉ ተግዳሮቶችን በማለፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና የውሃ ሀብትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብርና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነውም ብለዋል።

የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭን ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቀጠናዊ ተቋም በማሸጋገር በተፋሰሱ ላይ ዘላቂና ፍትሀዊ የውሃ አጠቃቀምን ለመምራት በፈረንጆቹ 2010 የተደረሰውን የትብብር ማዕቀፍ ያልፈረሙ አባል ሀገራት እንዲፈርሙ ዶ/ር ፍሎሬንስ ጥሪ አቅርበዋል።

የትብብር ማዕቀፉ ከወንዝ ጉዳይ ባለፈ ለአካባቢው ሀገራት ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

Share this Post