የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የገጠር ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው፡፡

የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የገጠር ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው፡፡

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የገጠር ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገለፁ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ የውይይት መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት የሀብት ብክነትን በመቀነስ የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የገጠር ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደ ዓለም ባንክ የመሳሰሉት የልማት አጋር ድርጅቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል። በሌላ በኩል ዩኒሴፍና የሚያስተባብራቸው የልማት አጋር ድርጅቶች በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቅሰው ለሚያደርጉትም ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በውይይቱ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ፣ በኢነርጂ ዘርፍና ሰብአዊ በሆኑ ድጋፎች ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር አለም ባንክና ዩኒሴፍን ጨምሮ በሀገር ውስጥ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ከመንግስት ጋር ተናቦ ለመስራት ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ውይይት መደረጉ ጠቃሚ መሆኑን የክቡር ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ ገልፀዋል።

በተቋሙ የኤሌክትሪፊኬሽንና የኢነርጂ መሪ ስራ አስፈፃሚ የኃይል ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ዳቢ እንደገለፁት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በተለያዩ ቦታዎች በድርቅና በግጭት ምክንያት የውሃና የኤሌክትሪክ እጥረት ያለባቸው ቦታዎች አገልግሎቱን እንዴት ተደራሽ እናድርግ በሚለው ዙሪያና ከባለድርሻዎች ጋር እንዴት እንስራ፤ እንደ ኢትዮጵያም ያለው ችግር በመቅረፍ የመጠጥ ውሃና የኢነርጂ ተደራሽነትን እንዴት ማስፋት ይቻላል በሚለው ዙሪያ በመወያየት ውጤታማ መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ልማታዊ ድርጅቶችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

Share this Post