የህዳሴ ግድብ እምቅ ሀብትን ለብልጽግና የማዋል ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኢፌድሪ ም/ጠ ሚኒስትር

የህዳሴ ግድብ እምቅ ሀብትን ለብልጽግና የማዋል ትልቁ ማሳያ ነው፡፡

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የኢፌድሪ ም/ጠ ሚኒስትር

መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 13ኛው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት በዓል "በህብረት ችለናል" በሚል መርህ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌድሪ ም/ጠ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እምቅ ሀብትን አውጥቶ ለብልጽግና ማዋል የመንግስት ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንና የዚህ ማሳያ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 13 ዓመታት በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ልዩነት በጋራ በመተባበር በተደረገው ጥረት ራሳችን በራሳችን የማልማት ጥበባችን ወደ ራሳችን መልሰናል የሚሉት ም/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማታችንን የማይፈልጉ ሀይሎች መሰረተቢስ ምክንያቶችን በማንሳት ለማደናቀፍ ቢታገሉም ፣በአለም መድረኮች ቢከሱም ሊያስቆሙን ግን ባለመቻላቸው አለም አቀፍ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

በዲፕሎማሲው ሂደት ፈተናዎችን ማለፍ የተቻለው እንደ አድዋ ዘመቻ በህብረ ብሔራዊ አንድነት በመነሳታችን ነው ያሉት ም/ጠ ሚኒስትሩ አሁንም የሚገጥሙንን የሰላምና ከድህነት የመውጣት ትልቅ ፈተናዎች በህብረ ብሔራዊ አንድነት ከተነሳን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የምንደርስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል፡፡

በቀጣይም የግድቡን ፍጻሜ ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ ያለሰለሰ ጥረት ማደረግ እደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የኢትዮጵያ ወንዞች ለዘመናት ለም አፈራችን እያጠቡ፣ እያራቆቱና በወንዞቹ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ከቀያቸው እያፈናቀሉ ለዘመናት ሲፈሱ መኖራቸውን አስታውሰው በዚህም ኢትዮጵያውያን በቁጭት በመነሳሳት የተለያዩ አነስተኛ ግድቦችን መገንባት ቢቻልም ከሀገሪቱ የውሃ ሀይል የማመንጨት አቅም አኳያ ሲታይ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው የዛሬ 13 ዓመት መጋቢት 24/2003ዓ.ም በኢትዮጵውያን የተባበረ ክንድ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ታሪክ ተሰራ ብለዋል፡፡

መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ትልቁ ወንዛችን ያለማንም ከልካይ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚያደርገውን ፍሰት ቆም ብሎ እንዲያስብ እና ለዜጎቹ ተገቢውን አገልሎት እዲሰጥ ለማድረግ በአባይና በኢትዮጵያውያን መካከል ቃለ መሃላ የተፈጸመበት እለት ነው ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ፡፡

ያለፉት 13 ዓመታት ጉዟችን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ለጋራ አላማና ተጠቃሚነት በጋራ መቆም እንደምንችል ያሳየንበት፣ የይቻላል መንፈስን ያረጋገጥንበት፣በወንዞቻችን ላይ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታችን ለአለም ማህበረሰብ ያሳየንበት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በመጀመሪያዎቹ 6 እና 7 ዓመታት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ችግር ቢገጥመውም በለውጡ መንግስት ድጋፍና ክትትል ህዳሴ ግድብ ህዳሴ ሆኖ እንዲቀጥል በልዩ ጥበብና ብልሃት ተመርቷል ብለዋል፡፡

በሂደቱ ለተወሰዱ የማስተካከያ ርምጃዎችና ፈጣን ውሳኔዎች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ሚናም ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትሩ ገለጻ ከ13 ዓመታት በፊት የተገባው ቃለ መሃላ ተፈጽሞ ፤አባይን በሚፈለገው መጠን ይዘን፤ በምንፈልገው ጊዜ ተጠቅመን፤ በምንፈልገው ጊዜ የመልቀቅ ደረጃ በመድረስ አባይን ማስተዳደር ችለናል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ይህ ልምዳችን በቀጣይ የውሃ ሀብቶቻችን ለማልማትም ሆነ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከፍተኛ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 95.8 ፐርሰንት እንዲደርስ ላለፉት 13 ዓመታት የገንዘብ፣ የጉልበት እንዲሁም ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ ዜጎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ያሰራው የህዳሴ ግድብ የመታሰቢያ ቴምብር ለ192 ሀገራት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራበት ይፋ ተደርጓል።

በእለቱ እስካሁን በነበረው የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ፣ የህብረተሠቡ ተሳትፎ ፣የነበሩ ጥንካሬዎች ፣ችግሮች እንዲሁም የግድቡን ፍጻሜ አስመልክቶ ፖናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከዙሁ ጎን ለጎንም የህዳሴ ግድብን የ13ዓመት የጉዞ ሂደትን የሚያሳይና እና ለ አንድ ሳምንት የሚቆይ ኤግዚቢሽን በኢፌድሪ ም/ጠ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተመርቆ ለዕይታ ክፍት ተደርጓል።

Share this Post