በብሄራዊ የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም እና በሌሎች የውሃ ሀብት አስተዳደር በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
ታህሳስ /2016 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በብሄራዊ የተቀናጀ ውሀ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም እና በሌሎች ዘርፉን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊዎችና የውሃ ሀብት አስተዳደር የስራ ክፍል ሀላፊዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቶቻችንን በጋራ የማልማትና የመጠቀም ሂደት አስፈላጊነትና በልዩ ልዩ የውሃ ተጠቃሚዎች መካከል አጠቃቀም ላይ መግባባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ እንደማሳያም ባለፉት አመታት የተተገበረው የቆላ ስንዴ መስኖ ልማት የገጠሩ ህብረተሰብ የመስኖ ጥቅምን መረዳት መቻሉንና በዚህም በእያዳንዱ ወንዝ ላይ ሰዎች እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም የውሃ ሃብት አጠቃቀም በአግባቡ እንዲመራ የዘርፉ ተዋናዮች ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፤ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መሰል መድረኮች ጠቃሚ ናቸው ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ የውሃ ጥራትን በማስጠበቅ፤ መጠኑን በማወቅና በውሃ ምደባ አሰራር ተደራሽ በማድረግ፤ እንዲሁም የወንዝ ዳርቻን በማስጠበቅ፤ የእንቦጭ ስርጨት በመግታት፤ በተለይ በባቱ፣ ጣናና ሌሎች ተፋሰሶች ያሉትን ችግሮች ምን ብናደርግ እንፈታቸዋለን የሚለውን መልስ ለማግኘት በኛ መካከል መግባባትና መናበብ ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በመጨረሻም ዘላቂ የውሀ ሀብት አስተዳደር ተጠቃሚዎችን መቆጣጠርና ማስተዳደር በሁሉም ክልሎች ወጥነት ባለው አግባብ መተግበር እንዳለበት በመግለጽ መርሀግብሩን አስጀምረዋል፡፡
መርሀ ግብርሩ ላይ በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የውሃ ሀብት አስተዳደር በኢትዮጵያ በሚል የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን፤ በዚህም የተቀናጀ ውሀ ሀብት አስተዳደር የነበረበትን እና አሁን ያለበትን ሁኔታ ደረጃ በደረጃ ገለጻ ያድረጉ ሲሆን፤ በተለይ በኢትዮጵያ ውሀን መጠቀም፤ ማልማት፤ መጠበቅና መቆጣጠር በሚቻልበት እና በሌሎች ውሀ ነክ ተግባራቶች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመርሀ ግሩ ላይ ብሄራዊ የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ላይ በዶክተር ብዙነህ አስፋው ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ በውሀ ሀብት አጠቃቀም ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጭምር ገልጸዋል፡፡
መድረኩ የሁለት ቀናት ሲሆን፤ ክልሎች ስራቸውንና ያጋጠማቸውን ችግሮች እንደሚያቀርቡም ከአስተባባሪዎች መረዳት ችለናል፡፡