የአፍሪካ ቻይልድ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት በሚኒ-ግሪድ ታሪፍ ማስያ መተግበሪያ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።
የአፍሪካ ቻይልድ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት በሚኒ-ግሪድ ታሪፍ ማስያ መተግበሪያ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።
16/10/2018 ዓም(ው.ኢ.ሚ)የአፍሪካ ሚኒ ግሪድ የኢነርጂ ተቆጣጣሪዎች (AFUR) የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና በሚኒ-ግሪድ (Mini-grids) ልማት ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ ስልጠና እየሰጠ ነው።
በስልጠናው ላይ የተገኙት በዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዩኤን ዲፒ የአፍሪካ ቻይልድ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ይመስላል ተፈራ ስልጠናው በዘርፉ ያሉ የቁጥጥር ማዕቀፎችን፣ ምርጥ ተሞክሮዎች እና የታሪፍ አወሳሰን ስልቶችን ያካተተ ሲሆን ተሳታፊዎች የቴክኒክና የፋይናንስ መረጃዎችን ወደ ስራ በመቀየር ረገድ ያላቸውን እውቀት ያሳድጋል ብለዋል።
በተለይም የፕሮጀክቶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደ የውስጥ መመለሻ ምጣኔ (IRR) እና የተጣራ የአሁኑ ዋጋ (NPV) ያሉ ወሳኝ የፋይናንስ መለኪያዎችን ማስላትን ጨምሮ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም (ATP) እና ፍላጎት ያገናዘበ ፍትሃዊ የታሪፍ ቀመር ማውጣት የሚያስችሉ ግንዛቤዎች ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል ።
በፕሮጀክቱ ያልተጠበቁ የወጪ መዋዠቆችን ለመቋቋም የሚያግዝ የስጋት ትንተና (Sensitivity Analysis) አሰራር ስርአት በስልጠናው ተካቷል።
የስልጠናው መርሃ ግብር ከአፍሪካ ሚኒ-ግሪድ ፕሮግራም (Africa Minigrids Program)፣ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና ከአለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ፈንድ (GEF) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሉክሰምበርግ እና በዴንማርክ መንግስታት ሙሉ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል ።
በስልጠናው ተሳታፊዎች በሁለት የሥራ ቡድኖች በመከፈል ለሁለት ሰዓታት የቆየ የተግባር ልምምድ ያደረጉ ሲሆን፣ ያዘጋጁትን የፋይናንስ ሞዴል፣ የገጠሟቸውን ስጋቶችና መፍትሄዎች፣ እንዲሁም ከየሀገራቱ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ግብ ጋር የሚጣጣሙ ስልታዊ እቅዶችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በስልጠናው ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የክልል ኢነርጂ ቢሮ፣ ከኤስ ኤን ቪ፣ ከጂአይ ዜድ ፣እንዲሁም ሌሎች አጋር ድርጂቶች የተውጣጡ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ።