በተከዜ ቤዚን የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እውን ለማድረግ ማሳያ ነው ተባለ።
ታህሳስ/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል /WLRC/ ጋር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እውን ለማድረግ በጋራ የሚተገብረው BRIGHT ፕሮጀክት በተከዜ ቤዚን የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ማሳያ ነው ተባለ።
ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል እና ብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ቡድን በጋራ የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስን ለማልማት በውይይት በቀረበው የዳሰሳ ጥናት መሠረት መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሀሪ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የገፀምድርና የከርሰምድር የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማስተዳደር በርካታ ስራዎች እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው፤ የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ የውሃ ሀብቱን በአግባቡ ፍትሃዊ ክፍፍል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በየቤዚኖቹ የሚያጋጥሙ ውሃ ነክ ችግሮችን ለመፍታት የቤዚን ፅ/ቤት ማቋቋም አስፈላጊ ነው ያሉት ዶ/ር ሚካኤል ውሃ ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎት መካከል አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ከመጠጥነት ባለፈ ለመስኖ፣ ለሀይል ማመንጫና ለተለያዩ አገልግሎቶች ስለምንጠቀምበት ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል ብለዋል።
ዶ/ር ሚካኤል አክለውም በፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ላይ በመስክ ምልከታ ያየነው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለሌሎች ቤዚኖች ጥሩ ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጠና አላምረው በበኩላቸው በንዑስ ተፋሰሱ የውሃ ሀብት አስተዳደር ምን ይመስላል የሚለውን ከቀረበው የዳሰሳ ጥናት ብዙ የተረዳን ቢሆንም መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አይተናል፤ በግድቦችም ያለ የውሃ ሀብትና የግጦሽ መሬት አያያዝ ለሌሎች ቤዚኖችም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው በንዑስ ተፋሰሱ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ዕቅዱን ወደታች በማውረድ በሙሉ አቅሙ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በመስክ ምልከታው የአካባቢው አርሶአደሮችም መስኖን ተጠቅመው ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረግ መቻላቸውን ገልፀው፤ የአየርንብረቱን መቋቋምና የገቢምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ችግኞችንም እንደሚያዘጋጁ ገልፀዋል።