የከርሰ-ምድር ውሃ ጥናት ዲዛይንና የጉድጓድ ቁፋሮ ቁጥጥር የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ሐምሌ 11/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍርካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ252.2 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ ክልሎች በአምስት አካባበቢዎች የከርሰምድር ውሃ ጥናት፣ ዲዛንና የጉድጓድ ቁፋሮ ቁጥጥር ለማካሄድ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት አድርጓል፡፡
የውል ስምምነቱን በተፈረመበት ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የጥናትና የጉድጓድ ቁፋሮ ቁጥጥር ስራዎቹ የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ውሃ አጠር አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጥናትና ቁፋሮ ቁጥጥር ስራዎቹ በፍጥነትና በጥራት መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ለስራው ውጤታማነት የተቋማችን የሚመለከታቸው ባለሙያዎች፣ አማካሪዎችና አመራሮች በቅንጅትና በትብብር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ዲዛይንና የጉድጓድ ቁፋሮ ቁጥጥር የሚተገበርባቸው አካባቢዎች፤ ይርጋለም አካባቢ፣ ሾኔ አካባቢ፣ ሁመራ አካባቢ፣ መተማና ጭልጋ አካባቢዎችና ታችኛው ኦሞ አካባቢ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የውል ስምምነቱ የተፈረመው ከአምስት አማካሪ ደርጅቶች ጋር ነው፡፡