ከ 4.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዳማ እና በባህርዳር ከተማ የፍሳሽ ማጣሪያና ማስወገጃ ግንባታ ውል ስምምነት ተደረገ፡፡
ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ4.6 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአዳማ እና በባህርዳር ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ግንባታ ለማከናወን የውል ስምምነት አደረገ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ፕሮጀክቱ ትልቅ በመሆኑ በቁርጠኝነት ከውሃ አገልግሎት እና ከክልል ውሃ ቢሮዎች ጋር ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚፈለገው ጥራትና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ስራውን አጠናቀው እንዲያስረክቡ አደራ ብለዋል፡፡
የአዳማውን ኮንትራት የፈረሙት የባይጌታ ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ታደሰ እና የባህርዳሩን ኮንትራት የፈረሙት የወገሬት ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ወርቁ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለሰጣቸው ዕድል አመስግነው በተያዘለት ጊዜ ገደብና በጥራት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
የባህርዳር ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ግንባታ ለማከናወን ከወገሬት ኮንስትራከሽን ኃ/የተ/የግ/ኩባንያ ጋር በ2,846,808,381 ብር ወጪ በ18 ወራት የሚጠናቀቅ ውል የተፈረመ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 1,086,534 ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ በቀን ከ300 እስከ 600 ሺህ ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻን የሚያጣራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የአዳማ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ግንባታ ለማከናወን ከባይጌታ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ኩባንያ ጋር በብር 1,804,084,655.89 ወጪ በ18 ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 1,040,734 ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ በቀን ከ400 እስከ 950 ሺህ ሊትር ፍሳሽ ቆሻሻን የሚያጣራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአዳማ እና በባህርዳር ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ግንባታውን ለማከናወን በአጠቃላይ 4,650,893,036.89 ከአለም ባንክ በተገኘ የብድር ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለ20 ዓመታት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
HYDROPLAN Ingenieur-HmbH የተባለ የጀርመን ኩባንያ አማካሪ ድርጅት የሁለቱንም ከተሞች የቁጥጥር ስራውን የሚያከናውን በመሆኑ የፍሳሽ ማጣሪያው ከኬሚካል ነፃ በሆነ መንገድ እርስ በርሱ ተብላልቶ በተፈጥሮ መንገድ የሚጣራ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ጉዳት በማያመጣ መልኩ ስለሚጣራ የፍሳሹ 70 በመቶ በአግባቡ ተጣርቶ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ወንዝ ወይም ወደ እርሻ ይቀላቀላል፤ 30 በመቶው ደረቅ ቆሻሻው ደግሞ ለማዳበሪያነት የሚያገለግል በመሆኑ በተደራጁ ሰው ኃይሎች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡