ከ2 ሺ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመተሃር ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ሰኔ19/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር በጋምቤላ ክልል ዋንቶዊር ወረዳ ከ2 ሺ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመተሃር ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ክቡር ዶክተር ጋትልዋክ ሪዮን የጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ በክልሉ የገጠር ከተሞችን የኤለክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግና የመንግስትን አቅጣጫ ለማስፈጸም በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የመተሃር ሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።
250 ኪሎዋት (kWp) ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው ና ከ96ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የተገነባው የመተሃር ሶላር ሚኒ-ግሪድ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ የማቅረብ አቅም ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅ እና በመንከባከብ እንዲጠቀሙ አደራ ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በፍትኃዊነት ለሁሉም ማህብረሰብ እንዲዳረስ የመከታተልና የመተግበር ኃላፊነት ያለው መሆኑን ገልጸው በሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶች፣ በትምህርት እና በጤና ተቋማት የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮጀክቶችን እንዲሁም በቤተሶብ የሶላር ሆም ሲስተም ቴክኖሎጅዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ከሚሆኑ ክልሎች የጋምቤላ ክልል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላላ እንደ ሀገር በመጀመሪያው ዙር ከሚገነቡት 100 ሶላር ሚኒ ግሪዶች ውስጥ ሶስቱ(3) በጋምቤላ ክልል የሚገነቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግንባታውን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው የሲቪል ስራዎች የተጀመሩበት ሂደት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ከተለዩት የገጠር እና በጣም ገጠራማ ወረዳዎች ውስጥ 13 በጋምቤላ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው በተቋማዊ የሶላር ሲስተም /Institutional Standalone
Solar System/ በክልሉ 2 የጤና ጣቢያ፣ 21 ሁለተኛ ደረጃ እና 8 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጠቅላላ 31 የትምህርትና የጤና ተቋማት በፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ እና ብርሃን ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ ሀገራችን ያለውን የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማስፋፋት ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የጸሀይ
ሀይል ማመንጫ በመገንባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናውኑ
ከሚነኙ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል።
ለፕሮጀክቶች ተግባራዊነት የተለያዩ ድጋፎችን ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢውን ማህበረሰብ አመስግነው የኃይል ማመንጫዎችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቁዋቸው አደራ ብለዋሌ።
የመተሃር ሶላር ሚኒ-ግሪድ 250 ኪሎዋት (kWp) ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው ና ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ የማቅረብ አቅም አለው።
በዝቅተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጊዜያት ያልተቋረጠ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚያስችል 60ኪሎ ቮልት አቅም ያለው ተጠባባቂ ጄኔሬተርን ያካተተ ፕሮጀክት ነውም ተብሏል።
የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቱ በመንደሩ ውስጥ ለሚገኙት 2500 አባወራዎች የመብራት አገልግሎት እንደሚሠጥም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ተወካይ እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር ገልጸዋል ።
በመርሀ ግብሩ የፌደራል ና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።