የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የውሃ ምንጮች ጥበቃ ለዘላቂ የውሃ አቅርቦትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ ናቸው።
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የውሃ ምንጮች ጥበቃ ለዘላቂ የውሃ አቅርቦትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ ናቸው።
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም.
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ የውሃ ምንጮች ጥበቃና በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ የውሃ ሀብት አስተዳደር የውሃ ጥራትን ለማሻሻል፣ የድርቅ ስጋትን ለመቀነስና ዘላቂ የውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው በሦስተኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት በቀረቡ ጥናታዊ ገለጻዎች ሲሆን፣ ጥናቶቹ የተፋሰስ መልሶ ማልማትን፣ የውሃ ምንጮች ጥበቃንና ዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂን ማቀናጀት ያለውን ፋይዳ አመላክተዋል።
በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል (WLRC) ዶክተር ይልቃል አንተነህ ባቀረቡት ገለጻ፣ በአባይ ተፋሰስ ከ2011 እስከ 2017 ዓ.ም. በተተገበረው የመማማሪያ ተፋሰሶች አቀራረብ 617 ሺህ 345 የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ የሥራ ቀናት ተከናውነዋል።
በዚህም የመኖ ምርት በሄክታር ከ20 እስከ 40 ቶን የደረሰ ሲሆን፣ የሰብል ምርታማነትም ከ15 እስከ 60 በመቶ መሻሻሉ ተጠቁሟል።
በጣና ሐይቅ ተፋሰስ በኩንዚላ ከ2020 እስከ 2024 ዓ.ም. በተተገበረው የተቀናጀ የውሃ፣ የመሬትና የንጽህና አገልግሎት ፕሮግራም 11 ሺህ 257 ሄክታር መሬትንና 36 ሺህ 752 ተጠቃሚዎችን ለማካተት ታቅዶ የተፋሰስ መልሶ ማልማት፣ ችግኝ መትከልና የውሃ ጥራት ክትትል ተከናውኗል።
እስከ 2025 በተደረገው ክትትል አማካይ የዝናብ ውሃ ፍሰት በ25.1 በመቶ፣ የደለል ምርት ደግሞ በ35.6 በመቶ መቀነሱ ተመላክቷል። በአንዳንድ የወንዝ ውሃ ናሙናዎች የፎስፌት መጠንም በ97.78 በመቶ ቀንሷል።
በተመሳሳይ፣ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የCR-WASH ዴስክ ዶክተር ተስፋ አክሊሉ በላይኛው አዋሽ ንዑስ ተፋሰስ ላይ ባቀረቡት ጥናት፣ ከተገመገሙ 2 ሺህ 965 የውሃ አቅርቦት መርሃ ግብሮች ውስጥ 1 ሺህ 124 ያህሉ ለከርሰ ምድር ውሃ ብክለት ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው አካባቢዎች እንደሚገኙ ተገልጿል።
ይህም የውሃ ምንጮችን ከብክለት ለመጠበቅ የጥበቃ ዞኖችን ማቋቋምና የውሃ ጥራት ክትትልን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያመለክታል።
በተጨማሪም፣ በጣና ተፋሰስ የቀረበው ጥናት የሳተላይት መረጃን፣ የማሽን መማር ቴክኖሎጂንና የሰብል ሞዴሊንግን በማቀናጀት የድርቅ ስጋትን በቅድሚያ ለመገመትና የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ያላቸውን ፋይዳ አሳይቷል።
በጥናቱ መሠረት፣ ጠብታ መስኖ ከቦይ መስኖ ጋር ሲነጻጸር 24 በመቶ ያነሰ ውሃ በመጠቀም 2.6 እጥፍ ከፍ ያለ የውሃ ምርታማነት አሳይቷል።
ከ2024 እስከ 2028 ዓ.ም. በአምስት የውሃ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትን ለማስፋት የተጀመረው BRIGHT ፕሮግራምም የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ማልማትን፣ የውሃ ማቆያ መዋቅሮችን መገንባትና የንጹህ ውሃ አገልግሎትን ማስፋት በማቀናጀት የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ ነው።
በአጠቃላይ፣ በአባይ፣ በጣና ሐይቅና በላይኛው አዋሽ ተፋሰሶች የቀረቡት ጥናቶች የተፋሰስ ሀብቶችን በዘላቂነት ማልማት፣ የውሃ ምንጮችን ከብክለት መጠበቅ፣ ዘመናዊ የመስኖ ሥርዓቶችን ማስፋፋትና በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፉ ውሳኔዎችን ቸግባራዊ ማድረግ ለዘላቂ የውሃ አቅርቦት፣ ለግብርና ምርታማነትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ መሆናቸውን አጉልተዋል።