የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎት ልየታ ማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ
የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎት ልየታ ማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ
ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎት ልየታ ማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ።
የአገልግሎት ልየታው ዋና ዓላማ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ለዜጎችና ለተገልጋዮች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በግልፅ መለየት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን መፈተሽ፣ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን መለየትና ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት ለዜጎች ማቅረብን ማረጋገጥ ነው።
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሌ፣ ሥራውን ሲጀምሩ የነበረው ግንዛቤ በሂደት እየዳበረ መምጣቱን ገልፀዋል። ይህም የዘርፉን አገልግሎቶች በተሻለ መንገድ በመለየትና በመደራጀት ለዜጎች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተጨማሪም የአገልግሎት ልየታው የተቋሙን የሥራ ሂደቶች ለማቀላጠፍ፣ ተደጋጋሚና አላስፈላጊ ሂደቶችን ለመቀነስ፣ የተገልጋዮችን ጊዜና ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ጠቃሚ መሠረት እንደሚሆን ጠቁመዋል። በዚህም ሥራ ላይ የተሳተፉትን የቡድን አባላት ላከናወኑት ሥራ አመስግነዋል።
በመቀጠል የአገልግሎት ልየታውን ያከናወኑት የቡድን አባላት በየተሳተፉበት የሥራ ዘርፍ የተገኙ ግኝቶችን፣ የታዩ ጥንካሬዎችን፣ የተለዩ ክፍተቶችንና ሊደረጉ የሚገባቸውን የማሻሻያ ሥራዎች በዝርዝር አቅርበዋል። እያንዳንዱ የቡድን አባልም በሥራው ሂደት ያጋጠሙ ልምዶችንና ለወደፊት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች በማንሳት ለመድረኩ ግብዓት ሰጥቷል።
በውይይቱም የአገልግሎቶችን ሂደት የበለጠ ማቀላጠፍ፣ የዲጂታል አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የተገልጋዮችን ተሳትፎና አስተያየት ማጠናከር፣ የተቋሙን ተጠያቂነትና ግልፀኝነት ማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቶችን ከዜጎች ፍላጎት ጋር ማጣጣም ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በመጨረሻም የቡድኑ አባላት የሥራውን ውጤት በማጠቃለል ቀጣይ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማስፈፀም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል። መድረኩም የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ በተገልጋይ ተኮር፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ተጠናቋል።