በጎርፍ አደጋ ምዘናና ሞዴሊንግ ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እየተካሄደ ነው
በጎርፍ አደጋ ምዘናና ሞዴሊንግ ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እየተካሄደ ነው
አርባምንጭ፣ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) — በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አዘጋጅነት፣ ከጣሊያኑ SWS Consulting Engineering እና ከሀገር ውስጥ ሬድዋን ሃይድሮሎጂ ሶሊውሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የአራት ቀናት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በአርባምንጭ ሀይሌ ሪዞርት ሆቴል እየተካሄደ ነው።
ከነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደው “Flood Risk Assessment, Modelling and Data Integration” ሥልጠና፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ፣ ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ከከተማ ልማት ሚኒስቴር እና ከተፋሰስ ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የቴክኒክ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ አባቡ፣ በጎርፍ አደጋ ምዘና፣ ትንበያና ቅነሳ ሥራዎች ውጤታማ ለመሆን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ ሳይንሳዊ የሞዴሊንግ ዘዴዎችን እና የተሟላ መረጃን መጠቀም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ፣ ሶፍትዌርና የሞዴሊንግ ዘዴዎች በፍጥነት በሚለወጡበት ወቅት የዘመኑን እውቀትና ተግባራዊ ክህሎት የተላበሱ ባለሙያዎችን ማፍራት የፕሮጀክቱ ትኩረት አንዱ ነው።
በዚህም ፕሮጀክቱ ከSWS Consulting Engineering እና ከሬድዋን ሃይድሮሎጂ ሶሊውሽን ጋር በጋራ በመሥራት ባለሙያዎች ዘመናዊ የጎርፍ ምዘናና ሞዴሊንግ እውቀት እንዲያገኙ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናውን አካሂዷል።
በሥልጠናው የተሳተፉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሃይድሮሎጂስት አቶ ታደለ ተስፋዬ፣ ሥልጠናው በጎርፍ አደጋ ምዘናና ሞዴሊንግ ዙሪያ የባለሙያዎችን ዕውቀትና ተግባራዊ ክህሎት ለማጎልበት ጠቃሚ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
አቶ ታደለ እንዳሉት፣ የሃይድሮሎጂ መረጃን በትክክል ማሰባሰብ፣ መተንተንና ከዘመናዊ የሞዴሊንግ መሣሪያዎች ጋር በማዋሃድ መጠቀም የጎርፍ ስጋትን በተሻለ ሁኔታ ለመገምገምና ለመተንበይ ያስችላል። ይህም በጎርፍ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና የአደጋ ምላሽ ሥራዎች ላይ የሚኖረውን አቅም ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
የሬድዋን ሃይድሮሎጂ ሶሊውሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሬድዋን ኑማን በበኩላቸው፣ ትክክለኛና ወቅታዊ የሃይድሮሎጂ መረጃን ማሰባሰብና በሞዴሊንግ ሥራዎች ላይ በአግባቡ መጠቀም የጎርፍ ስጋትን በተሻለ ለመገመትና ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናው ከመረጃ አሰባሰብና ትንተና ጀምሮ የጎርፍ ስጋትን በሞዴል እስከመገምገም ያለውን ሂደት በተግባር ለመረዳት እድል የፈጠረ ሲሆን፣ በጎርፍ ስጋት ምዘና፣ በጎርፍ ሞዴሊንግ፣ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ውህደት እና ዘመናዊ ሶፍትዌሮችን በጎርፍ ትንበያ ሂደት መጠቀም ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
የሥልጠናው ዋና ዓላማም በተሳታፊ ተቋማት ያለውን የቴክኒክ አቅም በማጠናከር የጎርፍ አደጋን በተሻለ ሁኔታ ለመተንበይ፣ ለመገምገምና ለመቀነስ የሚያስችል የባለሙያ አቅም መፍጠር ነው።
ይህ ዓይነቱ የተቋማት ትብብርና የባለሙያዎች አቅም ማጎልበት የጎርፍ አደጋን በቅድሚያ ለመለየት፣ የተሻለ ትንበያ ለመስጠት እና በአደጋ ጊዜ የሚደረገውን ምላሽ ለማጠናከር የሚያበረክት መሆኑ ተጠቁሟል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto