የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ሸበዲኖ ወረዳ ለሚያካሂደው የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር ዝግጅት ተጠናክሯል

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ሸበዲኖ ወረዳ ለሚያካሂደው የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር ዝግጅት ተጠናክሯል

ሲዳማ፣ ሸበዲኖ ወረዳ፣ ሀምሌ 29/2018 ዓ.ም

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር አካል በሆነው እና ነገ ሀምሌ 30/2018 ዓ.ም በሲዳማ ክልላዊ መንግሥት፣ በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን፣ በሸበዲኖ ወረዳ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የመጨረሻ ዝግጅቶች በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል።

በዚሁ መሠረት ለተከላው የተዘጋጁ ችግኞች ከማዘጋጃ ስፍራዎች ወደ ተከላ ቦታዎች በተቀናጀ ሥርዓት እየተጓጓዙ ሲሆን፣ ችግኞቹ በጥራት እንዲደርሱና በተያዘላቸው ቦታዎች በወቅቱ እንዲተከሉ አስፈላጊው ሎጂስቲክስና ቴክኒካል ዝግጅት ተጠናቋል።

መርሃ ግብሩ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነትን ከማጠናከር ባሻገር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን፣ የውሃ ምንጮችን ማስጠበቅን፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከልን፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምን እና የአካባቢ አረንጓዴነትን ለማሳደግ የሚያስችል ወሳኝ ተግባር መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማጣመር የማህበረሰብ ተሳትፎንና አንድነትን ለማጠናከር ያለመ መርሃ ግብር ነው።

በመርሃ ግብሩ የአከባቢ ነዋሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች እና ሌሎች የልማት አጋሮች በንቃት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ይህም የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ይሆናል።

በዝግጅቱ ክቡር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሚኒስቴሩ መካከለኛ አመራሮች፣ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች፣ የሲዳማ ክልልና የዞን አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመገኘት የችግኝ ተከላውን በጋራ እንደሚያከናውኑ ታውቋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብቶችን ለማስጠበቅና የውሃ ምንጮችን ለማልማት የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተፋሰስ ልማትን፣ የውሃ ምንጮች ጥበቃን እና ዘላቂ የአካባቢ ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተገልጿል።

Share this Post