በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረ የውሃ ምደባ ሰርዓት ለመገንባት ለባለድርሻ አካላት የሚዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
ሠመራ : ታህሳስ 21/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ ፍትሃዊ የውሃ ምደባ ስርዓት ለመገንባት ወሳኝ የሆነውን የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ የአዋሽ ተፋሰስ ለመስኖ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለግብርና ልማት የተሻለ እና ከሌሎች ተፋሰሶች ቀድሞ ወደ ልማት የገባ በመሆኑ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ በመንግስት፣ በግል ባለሀብቶችና በማህበረሰቡ ተሳትፎ የመስኖ ልማት የበለጠ የተስፋፋበት ነበር ብለዋል።
በተፉሰሱ የሚለማው የመስኖ መሬት ከ200መቶ ሺ ሄክታር በላይ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ የገለጹት ሀላፊው በዚህም ምክንያት ከሚያዚያ እሰከ ሰኔ ባሉት ወራት በተፋሰሱ የውሃ እጥረት ይከሰታል ብለዋል።
በመካከለኛውና ታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይ ደግሞ በክረምት ወቅት ጎርፍ የሚከሰት ሁኔታ መኖሩን የገለጹት አቶ ማሙሻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሰርዓትን በመዘርጋት እና የተፋሰስ ልማት እቅድ በማቀድ ጎርፍን ከአደጋ ስጋትነት ወደ ጠቃሚ ሀብትነት በመቀየር ውሃ በፈቃድ ላይ ተመስርቶ ፍትሃዊ ክፍፍል የሚደረግበት የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎችን በተሟላ መልኩ ለመፈጸም እንዲሁም በፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተ የውሃ ምደባ ስርዓት ለመገንባት በባዘርኔት ፕሮጀክት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ታቅደው እየተተገበሩ ሲሆን የዛሬው መድረክም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
በመድረኩ የጋራ ግንዛቤ እንደሚያዝና የኔነት ሰሜት እንደሚገነባ ያላቸውን አምነት የገለጹት ኃላፊው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ንቁ ተሳትፎ፣የበለጠ የትግበራ አቅም ፣ የበለጠ ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚጠብቅና ይህም በውይይቱ እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል።
የአፋር ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ በውሃ ምደባና ክፍፍል ፍትሃዊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተዘጋጀው መድረክ የተገኙትን በማመስገን በውይይቱ በሚገባ ተሳትፎ በማድረግ ቀጣይ ለሚሰራው ስራ የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩ ከፌደራል ፣ ከክልል ፣ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፣ ከዞን ፣ከወረዳ የመጡ ባለድርሻ አካላትና የሀገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉ ነው።