በ8ተኛው የበርሊኑ የኢነርጂ ሽግግር ውይይት ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ተሳተፉ፡፡

በ8ተኛው የበርሊኑ የኢነርጂ ሽግግር ውይይት ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ ሃገራቸውን ወክለው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡በጉባኤው  የ 50 ሃገሮች የኢነርጂ ሚንስትሮች በአካል ተገኝተው ሌሎቹ ደግሞ በድህረ ገጽ በቀጥታ እየተሳተፉበት ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከአፍሪካ ኢትዮጲያን ጨምሮ የ10 ሃገራት የውሃና የኢነርጂ ሚንስትሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ይህ አለም አቀፍ የኢነርጂ ጉባኤ  ዘንድሮ  ከምኞት ወደ ተግባር (from ambition to action) በሚል መሪ ቃል ሲሆን እየተካሄደ የሚገኘው በተለይ ታዳጊ ሃገራት ለዜጎቻቸው ኢነርጂ ለማቅረብ ያላቸውን ህልም ወደ ተግባር እንዲያወርዱት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታተት የሚመከርበት ነው፡፡

ኢትዮጲያ ባላት የህዝብ ቁጥር መሰረት ከፍተኛ የሃይል ፍላጎት በመኖሩ ይህም በኢነርጂ ልማት ለሚሰማሩ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ሰፊ የገበያ እድል በመሆኑ፤ ኢትዮጲያ ያካሄደችው የኢነርጂ ሴክተር ሪፎርም ፤ ታዳሽ ወይንም ከብክለት የጸዳ ሃይልን  ለማጎልበት ያላት ቁርጠኝነት፤  ምስራቅ አፈሪካን በሃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ያለውን ስራ መሰረት በማድረግ በዚህ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተሞክሮዋን እንድታቀርብ የተጋበዘች ሲሆን ክቡር ሚንስትሩም የሃገራቸውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡

ለዜጎች  ተመጣጣኝ፣ አስተማማኝ፣ ዘላቂ እና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለማግኘት ምን ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል? የኢነርጂ ተደራሽነት እና የብሔራዊ ፖሊሲ መፍትሄዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ከቋት  ውጪ ኃይል የማቅረብ  እርምጃዎችን   እንዲሁም  ከጎረቤት አገሮች ጋር ቀጠናዊ የሃይል ትስስርን እንዴት ማቀናጀት ይቻላል? በሚሉ ሃሳቦች ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ከጉባኤው  በተጓዳኝ ከተለያዩ ሃገራት አቻ ሚንስትሮች ጋር የኢትዮጵያን ብሎም አለም አቀፉን ወቅታዊ ሁኔታዎች በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Share this Post