የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሶስት ፕሮጀክቶችን ተፈራረመ፡፡
የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሶስት
ፕሮጀክቶችን ተፈራረመ፡፡
ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሶስት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በሁለት ክልሎች ለማስጀመር ተፈራረመ፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በሱማሌ ክልል ውሃ ስራዎችና ኮንስትራክሽን ድርጅት መካከል በሁለት ፕሮጀክቶች ላይ ስምምነት የተደረገ ሲሆን የመጀመሪያው በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኤረር ወረዳ የሚተገበር ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ድርቅን መቋቋም የሚችል የ 4 ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ እና ግንባታ ሥራ ሲሆን፤ ሌላኛው በተመሳሳይ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በቶጎጫሌ ከተማ ባለብዙ መንደር ድርቅን መቋቋም የሚችል የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ሲሆን፤ የሲቪል ስራዎችን፣ የውሃ ቧንቧና መገጣጠሚያ፣ እንዲሁም ኤሌክትሮሜካኒካል እቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎች ጨምሮ ከ490 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በእለቱ የውል ስምምነት የተደረገበት ሌላኛው ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጌድዮ ዞን የሚተገበረው የጨለለቅቱ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ የሲቪል፣ የውሃ ቧንቧና መገጣጠሚያ እና ኤሌክትሮሜካኒካል እቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎችን ጨምሮ ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት ተገልጿል፡፡የፕሮጀክት ስምምነቱ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በአበበ ነጋሽ ጠቅላላ ተቋራጭ መካከል ተደርጓል፡፡
ስምምነቶቹ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞና በድርጅቶቹ አመራሮች መካከል የተደረገ ሲሆን ክቡር ሚኒስትር ዲዔታው ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡