የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ። ጥር 24/2015 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በምርምርና አቅም ግንባታ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ እንደገለጹት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምርምርና ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር፤ በአቅም ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት የመስራትን አስፈላጊነትን አስምረውበታል። ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው አክለውም የውሃ ሀብታችንን መጠን ከመለየት፣ ጥራቱን ከመጠበቅና ከማስተዳዳር አኳያ፤ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማዳረስንና በገጠርና በከተማ የሳኒቴሽን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግን በተመለከተ፤እንዲሁም በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ላይ፣ በገጠር ኢነርጂ ማስፋፋት ላይ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና በቀጣይም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የመስራቱን አስፈላጊነት ገልጸዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የምርምር ስራዎች እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ በርካታ ስራዎች እያከናወነ እንደመገኘቱ መጠን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራቱ ጠቃሚ መሆኑን አውስተዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ በምርምርና ቴክኖሎጅ ልማት/ማላመድ ዙሪያ፤በዘርፉ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ፤የማህበረሰብ አገልግሎት ላይና የማማከር አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ከትብብር ስምምነቱ ጋር ተያይዞ በእለቱ በክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ በዶ/ር ሚካኤል መሃሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዋና ዋና ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞችን አስመልክቶ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን የምርምር ስራዎችና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በተመለከተ የኢኒስቲትዩቱ ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ደምስ አልማው ገለጻ አድርገዋል።

Share this Post