የእንቦጭ አረምን ከቆቃ ሀይቅ ለማስወገድ ከባለድርሸ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

የእንቦጭ አረምን ከቆቃ ሀይቅ ለማስወገድ ከባለድርሸ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡ ጥር/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የእንቦጭ አረምን ከቆቃ ሀይቅ ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባቱ ከተማ ውይይት ተካሄደ፡፡ በውይይት መድረኩ መክፈቻ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶክተር አብርሃ አዱኛ እንዳሉት የውሃ ሀብታችን በአግባቡ ለመጠቀም ከብክለት መከላከል፣ መጠበቅና ለልማት እንዲውል ማድረግ የተቋሙ ሀላፊነት መሆኑን ገልጸው ባለፈው ዓመት የተጀመረው ደንበል ሀይቅን ከእምቦጭ እና ሌሎች አረሞች ነጻ የማድረግ ስራ አመራሩ በበላይነት ይዞ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሚገባ በመመራቱ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡ እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ህይወት የሆነ ውሃ ህይወቱን ሲያጣ ህይወቱን ለመመለስ፤ ለተለያዩ ጥቅሞች ለማዋል፤ ከውሃ የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ብሎም ተፈጥሮአዊነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰራበት እንደሚገባና ባቱ ላይ የተሰራው የሀይቅ ደህንነት የማስጠበቅና የእንቦጭ አረምን የማስወገድ ተግባር በቀጣይ ቆቃ ሀይቅ ላይ ለሚሰራው ስራ ስንቅ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አረሙን ማጥፋት የሀይቁን ህይወት መታደግ እንደሆነ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ያሳሰቡት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አረሙን ለማስወገድ አማራጮችን ማሰብ እንዲቻል መድረኩ ወሳኝ መሆኑንና እስከመጨረሻው ቁርጠኛ ሆኖ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ መድረኩ ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማስፋት ብሎም ሀይቆቻችን የሀብት ምንጭ እና የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ በስፋት የምንወያይበትን እድል ያመቻቸ ብሎም ለቆቃ ሀይቅ ብቻም ሳይሆን ለአባያና ጫሞ ሀይቆችም ተሞክሮ የሚወስድበትና ወደ ልምድ በመቅሰም ወስደው እንዲተገብሩት መነቃቃትን የሚፈጥር ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ የእንቦጭ አረምን ምግቡን ከከለከልነው ታሪክ ሆኖ ይቀራል ያሉት የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ባለፈው ዓመት በደንበል ሀይቅ ላይ ያለውን የእንቦጭ አረም በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማስወገድ አመርቂ ስራ መስራት መቻሉንና በተያዘው ዓመትም ከባለፈው ልምድ በመውሰድ አመራሩ ግንባር ቀደም በመሆን ለሴክተር መስሪያ ቤቶች ስራውን አከፋፍሎ በመስጠት 80 ሄክታር የሚሸፍነውን አረም ሙሉለሙሉ የምናስወግድበት ምቹ ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡ ከንቲባው አክለውም አጠቃላይ ለእንቦጭ ምግብነት የሚሆኑትን ነገሮች በዘላቂነት ካስወገድን የውሃውን ደህንነት በማስጠበቅ የአሳ ምርት በሰፊው የሚጨምርበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና የተጀመረው የሀይቅ ዳር የመዝናኛ ፕሮጀክትም ከአረሙ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር እንደሚፈታም ተናግረዋል፡፡ በእለቱ የቆቃ ግድብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች፣ የእንቦጭ አረም ክስተት፣ ባህሪይ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ በቀረበ ጽሁፍ በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የውይይት መድረኩን በመሩት ክቡር ዶክተር አብርሃ አዱኛ የማጠቃለያ ሀሳብ የእለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል፡፡

Share this Post