ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን ፕሮግራም ሁለተኛ ዙር የፕሮግራም አጋማሽ አፈጻጸምና የመስክ ምልከታ ሪፖርት ቀረበ፡፡

ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን ፕሮግራም ሁለተኛ ዙር የፕሮግራም አጋማሽ አፈጻጸምና የመስክ ምልከታ ሪፖርት ቀረበ፡፡ **** ህዳር 19 /2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት የውሃ፣ የሳኒቴሽንና የሃይጂን (One Wash National Program) የፕሮግራም አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ መድረኩ የዋን ዋሽ ፕሮግራም ላይ መሰረት ያደረገ ምክክርና በቀጣይ በሚሰሩ ተግባራት ላይ በመምከር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በማሳደግ ሁሉም ዜጋ የንጹህ መጠጥ ውሃ በአቅራቢያው የሚያገኝበትን ስራ ለመስራት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሮግራሙ መንግሥት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋጋጥ ከያዛቸው የ10 አመት እቅዶች አንዱ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ይህን ፕሮግራም የሚደግፉ የውጭ አገር ለጋሾች የፕሮግራሙን እድገት እና እየተተገበሩ ያሉ ስራዎችን በመመልከት ድጋፋቸውን መቀጠላቸውን ጠቁመው በቀጣይም የተሻለ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ከፍ ለማድረግ መስራትና ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ማድረግ አለብን ብለዋል። በመድረኩ የተገኙት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው የመድረኩ አላማ ፕሮግራሙን በመተግበር ሂደት ላይ ከአፈፃፀም ጋር ተያይዘው የጋጠሙትን ችግሮች በመለየትና በማረም እንዲሁም በትግበራ ወቅት የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በመጠቀም በቂ የውሃ፣ የሳኒቴሽን እና የሃይጂን አገልግሎት ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘው ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የውሃና ኢነርጂ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመቀናጀት ፕሮግራሙን የተሻለ አፈፃፀም ደረጃ ማድረስ ያስችላል ብለዋል፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ 2019 ዓ.ም. የተጀመረና ከ14 ቢሊየን ብር በላይ የተበጀተለት ቢሆንም በኮቪድ-19፣ በአከባቢያዊ ፀጥታ ችግሮች የዘገየ ቢሆንም በቀጣዮቹ 2 አመት ተኩል ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል። የዋን ዋሽ ፕሮግራም በትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች የሳኒቴሽን እና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተፈጻሚ እያደረገ ያለ ሲሆን በመድረኩ በዋናነት ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በብድር አሰባሰብ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመድረኩ የክልል መንግስታት ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ኃላፊዎች፣ ከውሃ ቢሮ፣ ከትምህርት ቢሮ፣ ከጤናና የፋይናንስ ቢሮ የመጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራርሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Share this Post