በውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ውይይት ተካሄደ::

በውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ውይይት ተካሄደ። ህዳር/2015 (ው.ኢ.ሚ) የኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ መካከለኛ አመራሮች፣ የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤቶች አመራሮችና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራሮች ውይይት አካሂደዋል፡፡ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚንስትር ዲኤታ ክቡር ዶክተር አብርሃ አዱኛ እንደገለጹት ተቋሙ የውሃ ሀብትን ለማስተዳደር ከተጣለበት ኃላፊነት አንጻር በዘርፉ ሊተገበሩ የሚገባቸው ጉዳዮች የተፋሰስ እንክብካቤ፣ የውሀ ደህንነት ጥበቃ እና የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሀ መጠን ልየታ መሆኑን አውስተው እንደሃገር ውሃ ሀብትን መሰረት ያደረገ ልማት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማለትም፤ በስራ አመራር መሠረታዊ ነጥቦች የስራ ግንኙነት ማእቀፍ፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳዳር የስራ የግኘንኙት ማእቀፍ እና በሀይድሮሎጂና ተፋሰስ መረጃና የስራ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ የስራ አመራር መሰረታዊ ነጥቦችን አስመክቶ በቀረበው ጽሁፍ፤ ጥሩ የመሪና ተመሪ ግንኙነት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፤ ወጥነት ያለው የእቅድና ሪፓርት ስርዓት በመዘርጋት በ2022 ከሚደርስባቸው ግቦች ላይ በማተኮር መስራት እንዳለባቸው የአስተዳደር ዘርፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ ባቀረቡት ጽሁፍ ጠቁመዋል፡፡ በተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር እና የሀይድሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ አስተዳደር የስራ ግንኙነት ላይ ሰፊ ሰነድ የቀረበ ሰሆን በተለይ፤ በውሃ አካላት ደህንነት ጥበቃና ተፋሰስ ልማት ማሻሻል፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የውሀ አካላት ሽፋን ማሳደግ፤ በቤዚን ፕላን ዝግጅት፤ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማሳደግ፤ የትስስር ፎረም መመስረት፤ የውሃ ሀብት መረጃ የመሰብሰብ፡ የመተንተንና ተደራሽ የማድረግ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡ በሌላ በኩል የተቋማት ለውጥ ስራ አስፈጻሚ በዘርፉ የሩብ አመት የክትትልና ግምገማ ግብረ መልስ ሪፓርት የቀረበ ሲሆን በክትትል ወቅት ያታዩ አበረታች እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ቀርቧል፡፡ ውይይቱ ላይ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤቶችና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የመጡ መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Share this Post