የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በባህር ዳር ተጀመረ።

የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በባህር ዳር ተጀመረ። ባህር ዳር፤ መስከረም 5/2014 ዓ.ም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዉሃ፣ የዉሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በባህር ዳር ዩኒቨርሰቲ ዊዝደም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው። መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት አብዛኞቹ በሀገራችን የሚገኙ ወንዞች ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚፈሱ መሆናቸውን ገልጸው የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ለማልማትና ለመጠቀም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ መወሰዱንና ሀገራችን የተጠቃሚነት መብት ለማስከበር በርካታ የትብብርና የድርድር ሂደቶች ውስጥ እየታለፈ መሆኑን ገልጸዋል። ክቡር ሚንስትር ዴኤታው በመቀጠል የዉሃ ሀብታችንን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑንና ከዉሃ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ የሀሰት ትርክቶችን እና የተዛቡ መረጃዎችን ለማስተካከል ፎረሙ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ተሳታፊዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በዉሃ፣ ዉሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች መማክርት ፎረም ላይ ላቅ ያለ ሚና መጫወት የሚችል ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አውስተው መድረኩ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪመ በዩኒቨርሲቲው የተመሰረቱ የተለያዩ ትስስሮች መሰል ፎረሞችን የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል። “የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም” በውሃና ኢነርጂ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ሙሁራንን፣ የሀይደሮ ዲፕሎማሲ ሙሁራንን፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የድርድር ሂደት የተሳተፉ ተደራዳሪዎችንና ባለሙያዎችን፤ እንዲሁም የኮሚኒኬሽንና የሚዲያ ባለሙያዎችን በማካተት በዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተመሰረተ ነው፡፡ ፎረሙም በዋነኛነት ከውሃ ሀብትና ከኢነርጂ ሀብት ልማት አንጻር፤ እንዲሁም ከሕዳሴው ግድብና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞቻችን ጋር በተያያዘ በዘርፉ ሙሁራን፤ በዘርፉ ተዋናዮችና በሚዲያ አካላት መካከል ሊሠሩ በሚገቡ ሥራዎች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ይመክራል፤ ፎረሙ በርካታ በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች የሚሳተፉበት መድረክ ነው።

Share this Post