የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አተገባበር ላይ ምክክር ተካሄደ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አተገባበርን በተመለከተ በአዳማ ከተማ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አተገባበርን በተመለከተ ከክልል ውሃ ቢሮዎችና ከአጋር አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ምክክር ተካሄደ፡፡ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍን በመወከል የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ ሃይማኖት በለጠ፤ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማት አስተዳደደር ዳይሬክተር እንደገለጹት የመጠጥ ውሃ ተቋማት ዘላቂነት ባለው መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ከውሃ መገኛ እስከተጠቃሚው በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተዳደር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የውሃ ደህንነት እቅድ ትግበራ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ በክልሎች፣ በተመረጡ ከተሞችና በገጠር አካባቢዎች በትግበራ ወቅት አበረታች ውጤት መታየቱን ገልጸው፤ ትግበራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ሌሎች አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ፤ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል የውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አተገባበርን በተመለከተ የተደረጉ የመስክ ቅኝቶችንና ጥናቶች በምክክር መድረኩ የሚቀርቡ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ክልሎች፤ ከተማ አስተዳደሮችና ውሃ አገልግሎቶች የውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አካቶ (Water safety plan mainstreaming) ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውና በእቅድ ውስጥ ተካቶ መያዝ እዳለበት አውስተዋል፡፡ በሌላ በኩል መድረኩ መሰል እቅዶችን ለመተግበር ከአጋር አካላት ጋር አብሮ ለመስራትና የሚጠበቀውን ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተግዳሮቶችና የአየር ንብረት ለውጥ ሊቋቋም የሚችል የመጠጥ ውሃ ተቋማት ደህንነት እቅድ አተገባበርን በተመለከተ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ትናንት የተጀመረው የምክክር መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን የክልል የውሃ ቢሮዎች፣ የከተሞች የውሃ አገልግሎቶችና አጋር አካላት በመድረኩ በመሳደተፍ ላይ ናቸው፡፡

Share this Post